arrow_back Back to News • Jun 03, 2026

ክፍል 4፦ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ሲደረግ የመጀመሪያው ትኩረት የሚሰጠው

Source: softcover

ክፍል 4፦ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ሲደረግ የመጀመሪያው ትኩረት የሚሰጠው
  1. የማስነሻና የመጠቆሚያ መሣሪያዎች (Starting & Instrument Panel)

    በባቡር ሐዲዶችና በጠባብ መንገዶች ላይ በምናሽከረክርበት ጊዜ ሞተሩ በድንገት ቢጠፋ በአፋጣኝ ሞተሩ በማስነሻው የማይነሣ ከሆነ የሚደርሰው አደጋ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ መሣሪያ በምርመራ ጊዜ ትክክለኛነቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

    የመጠቆሚያ መሣሪያዎች ያለውን የነፋስ መጠን፣ የዘይት ግፊት፣ ዲናሞ ወይም ኦልተርኔተር ባትሪውን በትክክል መሙላቱን፣ የራዲያተር የውሃ ሙቀት መጠንና የተሽከርካሪውን የፍጥነት ልክ የሚያሣይ መሆን አለበት፡፡ የፍጥነት ወሰን መከታተያ (Speedometer) በትክክል መሥራቱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡

  2. የመብራቶች እና የደህንነት መለዋወጫዎች ዝርዝር መስፈርት

    የግንባር መብራቶች (Head Lights)፦ ብርጭቆዎቻቸው ያልተሰበሩ፣ በቂ ብርሃን የሚሰጡ፣ ቀለማቸው ነጭ የሆነና በቂ ርቀት የሚያሳዩ መሆን አለባቸው። በሚሠሩበት ወቅት ብርሃናቸው ወደላይና ወደጎን ከመንገድ ውጪ መሆን የለበትም። እንደ አስፈላጊነቱ አጭር ወይም ረዥም በአንድ ላይ ሁለቱም ሊለዋወጡ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

    የማቆሚያ መብራቶች (Parking Lights)፦ በጨለማ ጊዜ ተሽከርካሪያችን ከመንገድ ዳር አቁመን በምንሄድበት ጊዜ የማቆሚያ መብራት መሥራት አለበት፡፡ ይህም በግልጽ የሚበራና ብርጭቆዎቹም ያልተሰበሩ ነጭ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

    የፍሬቻ መብራቶች /አቅጣጫን የሚያመለክቱ/ (Directional Light)፦ ብርጭቆዎቻቸው ያልተሰበሩ፣ ያልተሸረፉና ቀይ መብራት ያላቸው፣ ሁለቱም የሚበሩና ከበቂ ርቀት የሚታዩ መሆን አለባቸው፡፡

    የፍሬን መብራቶች (Stop Lights)፦ ብርጭቆዎቻቸው ያልተሰበሩ፣ በእግር ፍሬን የሚታዘዙና ሁለቱም ደማቅ ቀይ መብራት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

    የሠሌዳ መብራቶች (Plate Light)፦ ከሠሌዳው አጠገብ የሚገጠሙ፣ ብርጭቆው ያልተሸረፈና ነጭ መብራት የሆነ እንዲሁም በጨለማ ጊዜ ቁጥሮቹን በትክክል የሚረጭ (የሚያሳይ) መሆን ይኖርበታል፡፡

    የዝናብ መጥረጊያ (Windshield Wiper)፦ በበቂ ፍጥነት የሚጠርጉ፣ ላስቲካቸው ያልተበላና ሙሉውን መስተዋት የሚጠርጉ መሆን አለባቸው። ቢቻል የውሃ መርጫ ኖሮት በትክክል የሚረጭ መሆን ይኖርበታል፡፡

    የፀሐይ መከላከያ (Sun Visor)፦ የፀሐይ ጨረርን ሊከላከሉ የሚችሉ፣ የፀሐይ ጨረር በሌለበት ጊዜ ሊታጠፉ የሚችሉ፣ ያልተቀደዱና ያልተሰበሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡